• Skip to content
  • Jump to main navigation and login

Nav view search

Navigation

  • Home

Search

You are here: Home

ከየት ልጀምር?!

በአሜሪካን አገር በሚገኝ አንድ ትልቅ ዪኒቨርሲቲ ውስጥ ተመራማሪ ሆኜ እየሠራሁ እገኛለሁ። አልፎ አልፎም ሁኔታዎች ሲያመቹ በዚያው ዪኒቨርሲቲ ውስጥ አስተምራለሁ። ከዚህ በፊት በሁለት የተለያዩ ዪኒቨርሲቲዎች ውስጥ በምርምር ሥራና በአስተማሪነት  አገልግያለሁ። ዛሬ ያለሁበትን ሁኔታ የሚያይ ሰው ከየት እንደተነሳሁ ለማሰብ የሚቸገር ይመስለኛል። መንገዴ ግን በእግዚአብሔር የተቆረጠ ስለነበር ጥሻውን አልፌ ያለሁበት ደርሻለሁ።ተወልጄ ያደግሁት አምባሰል ነው። የአምባሰልን ተራራ ዝናውን ሰምተው ዘፋኞች ብዙ ተቀኝተዋል። አምባሰል ለገደል መች ያሽሟጥጡታል ፈረስ ባይወጣበት ሰው ይወጣበታል ተብሎ ተዚሞለታል።ሰው የተወለደበትን ከተማ የትውልድ ቦታው አድርጎ መጥራቱ የተለመደ ነው። መወለድን የተወለድኩት ደሴ ህፃናት ሆስፒታል ነው። ነገር ግን የተሻለ ሕክምና ፈልጋ እናቴ ደሴ ወለደችኝ እንጂ ከጽንሰት እስከ ልጅነት የኖርኩት ግን ወይናደጋ የአየር ጸባይ ባላት በውቧ የውጫሌ ከተማ ነው። የለጋነት ዕድሜየን ጥንቅሽና ሸንኮራ አገዳ፣ ፉላና ቁርቁራ፤ ፓፓያና ትርንጎ የመሳሰሉትን የተፈጥሮ ስጦታዎች ከተለመደው እንጀራና ወጥ ጋር እየተመገብኩ ያደኩባት ከተማ ናት። ድሽቅ፤ ደኑ ገላና ቁንጥሮ፤ ኳስ የምንጫወትበት ብጭር ሜዳና የሽቦ መኪና ለመሥራት ሽቦ ፍለጋ የምንሄድበት ድስሚት፤ ለኳስ ጨዋታ በእግር ተጉዘን የምናያት ውርጌሳ፤ ዋና ለመዋኘት የምንለማመድበት የጎሎ ወንዝና የቀልጣ ጅረት፤ ፍራፍሬ ለመግዛት በእግር ተጉዘን የምንሄድባት ጢስ አባሊማ፤ ሽቅብ እያየን ዘወትር የምንገረምበት የአበት ተራራ፤ በሩቅ እያየን የምንናፍቀው የድብል አናት በልቤ ማኅደር ያስቀመጥኳቸው መልካም ትዝታዎቼ ናቸው።

 

 

Powered by Mehary Tadesse Ph.D.